በመዲናዋ የመድሐኒት አቅርቦት ችግር መኖሩን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚዎች ገለጹ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ የጤና ተቋማት ላይ የመድሐኒት አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮች መኖራቸውን የከተማዋ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡
በከተማዋ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚዎች በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ፣በቂርቆስ ክ/ከተማ፣ በቦሌ ክ/ከተማና በየካ ክ/ከተሞች በሚገኙ የጤና ተቋማትና ከነማ ፋርማሲዎች ላይ መድሐኒት የለም እንደሚባሉ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም እንደሚጉላሉና አተገባበሩ ላይም ችግር እንዳለ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዳይሬክተር አቶ ኢብራሂም ተካ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ÷በጤና ተቋማት የሕክም ግብዓቶች ተሟልተው አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በከተማዋ በመተግበር ላይ በሚገኘው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን÷ ተጠቃሚዎች በመንግስት የጤና ተቋማት አገልግሎት እንደሚያገኙም ጠቅሰዋል፡፡
ከነማ ፋርማሲ ትልቅ አጋር መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፥ በአንድ አመት ከ100 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች በከነማ ፋርማሲ አገልግሎት እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡
በከነማ ፋርማሲዎች ላይ የሙያ ሥነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ባለሙያዎች ላይም እርምጃ መወሰዱን ነው የሚናገሩት፡፡
በተጨማሪም ክፍተት ያለባቸውን ቦታዎች በመለየት ለባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ አንደሚገኝ ጠቅሰው፥ ክትትልና ድጋፍም እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አንዳንድ የጤና ተቋማት ላይ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው÷ በተቻለ መጠን መሻሻሎች እየመጡ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የጤና መድሕን አገልግሎት መርሐ ግብር ግለሰቦች በአመት አንድ ጊዜ ወጪ በማውጣት የጤና እክል ሲገጥማቸው የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበትና ካልታሰበ ወጪ የሚድኑበት መንገድ ነው፡፡
በየሻምበል ምህረት