Fana: At a Speed of Life!

የቤት አቅርቦት  እጥረትን ለመፍታት የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራሞችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማ ቤት አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራም አማራጮችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ÷ የከተማ፣ መሬትና መሬት ነክ ንብረት ይዞታን መዝግቦ ዜጎችን ሕጋዊ ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የተጀመረውን ሕጋዊ የካዳስተር ስራ ውጤታማ ለማድረግ የሁሉም ክልሎች ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ የበጀት ዓመቱን የግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም የከተማ አስተዳድሮች የክልል የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት እየገመገመ ነው።

የከተማ መሬት ፕላንን እና የመሬት ልማት ማኔጅመንት ስርዓትን በማዘመን መሬት ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት የበኩሉን መወጣት የሚችልበትን ስራ ማከናወን ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች መልሶ በመገንባት እና በማቋቋም ረገድ ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ  መቆየቱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

የተገኘው ውጤትም ህዝባዊ ጥምረትና ህብረት የተስተዋለበት በመሆኑ የሚኒስቴሩን የተልዕኮ አቅም ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴሩ ቀዳሚ ትኩረት ከሰጣቸው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ በተሰራው ስራ 84 ከተሞች በዚህ ፕሮግራም እንዲካተቱ መደረጉን አመላክተዋል፡፡

አሁን ላይ ካለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት አንጻር ሲታይ ከድህነት ወለል በታች ያሉትን ዜጎች ከመደገፍ አንጻርም ትልቅ  እገዛን  ያደረገ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የከተማ ቤት አቅርቦት  እጥረትንም ለመፍታት የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራም አማራጮችን በመጠቀም ወደ ስራ መገባቱ ተገልጿል፡፡

በይስማው አደራውና ቤዛዊት ከበደ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.