Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ በጤና እና በምግብ ችግሯን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ነው – ሙሳ ፋኪ መሀመት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ በጤና እና በምግብ ችግሯን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀመት ተናገሩ፡፡

42ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ተጀምሯል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀመት በቱርክና ሶርያ በደረሰው ተፈጥሯዊ አደጋ ሀዘናቸውን በመግለፅ አስጀምረዋል።

አፍሪካ ጤና እና ሥነ ምግብ ቁልፍ የሕብረቱ ስራዎች አድርጋ በቀዳሚነት እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።

የአፍሪካ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል እና የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ መቋቋማቸው ይህን ጥረቷን ለማሳካት ብሎም ከጥገኝነት ለመላቀቅ እንደሚያስችላት ጠቅሰዋል።

በጤና አጠባበቅ እና በሥነ- ምግብ ራስን ለመቻልም አገራት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በኢኮኖሚ ረገድ አፍሪካ የንግድ ግብይት ለማሳለጥ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራም ለማፋጠን እየተሰራ ነው ማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአፍሪካ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት፣ ያላትን ሃብቶች አሟጣ ለመጠቀም፣ ዲጂታላይዜሽንን ለማፋጠን፣ የዕውቀት ሽግግር ለመፍጠር በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።

በአህጉራዊ ሰላምና ደኅንነት ረገድ ደግሞ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ የመፍታት ማዕቀፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት በሕብረቱ መሪነት ሰላም የማረጋገጥ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የውጭ ጣልቃገብነት የችግሮቹ መባባስ እንጂ መፍትሔ እንደማይሆን ገልፀው፣ በሱዳን፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በሊቢያ፣ በጊኒ ቢሳው፣ በሶማሊያ፣ በማሊ፣ በቡርኪናፋሶ የተከሰቱ የሰላም ችግሮች እንደሚፈቱ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን በድርድርና በሌሎች አማራጮች ወሳኝ ሚና ስለመጫወቱ አንስተዋል።

ሊቀመንበሩ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፍትሔ በሚለው መርህ አህጉራዊ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት እንዲፈቱ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ጥረቶችንም አባላቱና አጋር ሀገራት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በወጣቶችና ሴቶች ፋይናንስ አካታችነት ረገድ በተለይም የ2063 የአፍሪካ አጀንዳ ዕውን ለማድረግ በሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ተለዋጭ በሆነው ዓለምአቀፋዊ ፖለቲካ አፍሪካ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ የባለብዙ ወገን ትብብሮችን እንደምታጠናክር ገልፀዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.