Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎቱ 453 ሺህ 589 ጉዳዮችን በማስተናገድ 776 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሥድሥት ወራት 453 ሺህ 589 ጉዳዮችን በማስተናገድ 776 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
 
የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አለምሸት መሸሻ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በግማሽ ዓመቱ ለበርካታ ደንበኞች ተዓማኒ፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ስኬታማ አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡
 
በተለያዩ አገልግሎት ዘርፎች 53 ሺህ 406 ጉዳዮችን ለማስተናገድ ታቅዶ 453 ሺህ 589 ጉዳዮችን ማስተናገድ መቻሉን አንስተዋል፡፡
 
በዚህም 776 ነጥብ 8 ሚሊየን በመሰብሰቡ የዕቅዱን 147 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው ስራ አስፈጻሚው የተናገሩት፡፡
 
በግማሽ ዓመቱ ጥራት ያለው ሰነድ በማመንጨት በውልና ውክልና ዘርፍ 359 ሺህ 247 የሚሆኑ አገልግሎቶች በኦንላይን የአሰራር ስርዓት ታግዘው መሰጠታቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
ተገልጋዮች የሚያቀርቧቸው ሀሰተኛ ሰነዶች መበራከት የተቋሙ ተግዳሮት እንደነበር ጠቁመው÷ በድርጊቱ ጥፋተኛ የሆኑ ተገልጋዮች ላይ አስፈላጊው የህግ እርምጃ መወሰዱን አንስተዋል፡፡
 
በቀጣይ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አመላክተዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.