Fana: At a Speed of Life!

በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስተባባሪነት በመቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ተገጣጣሚ ቤቶችን ሊገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስተባባሪነት መቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ጊዜያዊ ተገጣጣሚ ቤቶችን ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ።

በመቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የምክትል ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ አሰፋ ባልኤር እንደተናገሩት መቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኙን ለመከላከል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ከመንግስት ጋር እያደረገ ይገኛል።

በማዕከሉ ከ2 ሺህ 500 በላይ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማንን እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ አሰፋ፤ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን በአንድ ቦታ ተሰባስበው መኖራቸው ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስተባባሪነት ፍቃደኛ የሆኑ የተለያዩ ኮንትራክተሮችን እና ባለሃብቶችን በማሳተፍ ጊዜያዊ ተገጣጣሚ ቤቶችን ለመገንባት ቦታውን የመጥረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ግምታቸው ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ ቁሳቁሶችን በስጦታ ማበርከቱን የጠቆሙት አቶ አሰፋ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ ማዕከሉ የሚመጡ እርዳታዎች እየቀነሱ በመሆኑ  በመተጋገዝና በመተባበር የደከሙ ወገኖቻችንን ልንደግፍ ይገባልም ነው ያሉት።

በተጨማሪም በቅርብ ጊዜ 2 ሺህ የሚሆኑ አረጋዊያንን ለማንሳት በመታሰቡ 8161 ላይ ok ብላችሁ በመመዝገብ ወይም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አጋርነታችሁን ልታሳዩ ይገባል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.