Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ በደረሰ የእሳት አደጋ 10 የንግድ ሱቆች ወደሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ቡልቡላ አካባቢ በተነሳ የእሳት አደጋ 10 የንግድ ሱቆች መቃጠላቸውን የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ የእሳት አደጋው ያጋጠመው ትናንት ሌሊት 7:51 ላይ ነው።

የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠርም 4 የአደጋ ጊዜ ተሽከርካሪ፣ አንድ አምቡላንስ እና 27 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞቾ ተሰማርተዋል ብለዋል።

አሁን ላይም የእሳት አደጋው ተስፋፍቶ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ውሏል ነው ያሉት።

በእሳት አደጋው በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ጠቅሰው፥ በንብረት ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን እና የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ገልፀዋል።

አሁን ያለንበት ወቅት (የአየር ጸባዩ) ለእሳት አደጋ መከሰትና መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ህብረተሰቡ እሳትና የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮችን ሲጠቀም ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

እንዲሁም አደጋ ሲያጋጥም ህብረተሰቡ በ939 የነጻ ስልክ መስመር ፈጥኖ እንዲያሳውቅ ተጠይቋል።

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.