Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ስፔን የ5 ዓመት የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ስፔን በቀጣይ አምስት ዓመት የኢኮኖሚ ትብብራቸው የሚመራበትን ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴና የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴ ማንኤል አልባሬስ ቤኖ ፈርመዋል፡፡

በስነ-ስርዓቱ አቶ አህመድ ሺዴ ÷ ኢትዮጵያና ስፔን ረጅም ጊዜ ያሰቆጠረ ግንኙነት እንዳለቸው ጠቅሰዋል፡፡

በአሁን ወቅት የስፔን መንግስት በዓለም አቀፍ የጤና ተደራሽነት፣ በአካታች የገጠር ልማትና በስርዓተ ፆታ ዕኩልነት እያበረከተ ያለውን ድጋፍም አድንቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ነድፎ ፈጣን ልማት ለማምጣት፣ የግሉ ዘርፍ በየኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ተሳትፎ እንዲጎለብትና አዳዲስና ነባር የኢንቨስትንት መስኮች እንዲስፋፉ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴ ማንኤል አልባሬስ ቤኖ በበኩላቸው ÷ አዲስ የተፈረመው የአምስት ዓመት የትብብር ማዕቀፍ የኢትዮጵያና ስፔንን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር አመላክተዋል፡፡

ስፔን ዓለም አቀፉን ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ከመንግስታት ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደምትገኝም መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የተፈረመው ስምምነት  ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ በጤና፣ በገጠር ልማት፣ በስርዓተ ፆታ እኩልነትና በሰብዓዊ ድጋፍ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን እንደሚያጠናክር ሆሴ ማኑኤል አስረድተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.