Fana: At a Speed of Life!

ከ18 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ወርቅ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ይዞ ሲወጣ ተይዟል የተባለው ቻይናዊ ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈቃድ ሳይኖረው ከ18 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ 3 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ይዞ ሲወጣ ተይዟል የተባለው ቻይናዊ ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡

በኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ፈቃድ ሳይኖረው ጥፍጥፍ ወርቅ እና ኮፐር፣ ዚንክና ሲልቨር የያዘ 2 ኪሎ ግራም የሚመዝን ማዕድን በህገ-ወጥ መንገድ ይዞ ሲወጣ መያዙን ገልጿል፡፡

ይሄን ተከትሎም በወንጀሉ ተጠርጥሮ የተያዘው ቻይናዊ ተከሳሽ ላይ የኮንትሮባንድ ወንጀል ክስ ተመሰርቶበታል፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ፓን ችዋን የተባለው ቻይናዊ ተከሳሽ ገደብ የተደረገበት መሆኑን እያወቀ (ማወቅ ሲገባው) የብቃት ማረጋገጫና ፈቃድ ሳይኖረው ማዕድናቱን ከሀገር ይዞ ሊወጣ ሲል መያዙ ተመላክቷል፡፡

የዋጋ ግምቱ 18 ሚሊየን 5 ሺህ 939 ብር የሚያወጣ ቀረጥና ታክስ 12 ሚሊየን 824 ሺህ 53 ብር የሚከፈልበት 3 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ እና 2ሺህ 196 ብር ቀረጥና ታክስ የሚከፈልበት በውስጡ ኮፐር፣ ዚንክና ሲልቨር የያዘ 2 ኪሎ ግራም የሚመዝን ማዕድን የሻንጣ የብረት ዘንግ ውስጥ አድርጎ ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና ሀገር ይዞ ሲወጣ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የወጪ መንገደኞች የደህንነት ኤክስሬይ መፈተሻ ቦታ ላይ መያዙም ተጠቁሟል፡፡

በዚህም በፈፀመው ገደብ የተደረገበት ዕቃን በህገ-ወጥ መንገድ ይዞ መውጣት የኮንትሮባንድ ወንጀል የማዕድን ግብይት አዋጅ ቁጥር 1144/2011 አንቀጽ 12/1/፣ 5፣ እና 36/1/ እንዲሁም የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 (በጉሙሩክ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1160/2011 አንቀጽ 2/44/ እንደተሻሻለው) አንቀጽ 168/1/ ስር የተደነገገውን ተላልፎ የኮንትሮባንድ ወንጀል መፈፀም ክስ ቀርቦበታል፡፡

ጉዳዩ የቀረበለት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎትም ተከሳሹ የተከሰሰበትን ክስ ለመስማት ለየካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.