Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቁ ይገባል – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል እየተከናወኑ ያሉ ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ።

የክልሉ ካቢኔ አባላት ጋር በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን ገምግሟል።

ከአው ኡመር የመንገድ ግንባታ ጋር ተያይዞ በቀረበው ሪፖርትም መንገዱን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከመንገድ ዳር ያሉ ቤቶች በተገቢው ጊዜ ያለመነሳትና ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች ለፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ አለመከናወን ዋነኛ ማነቆ መሆናቸውም ተገልጿል።

ሌላኛው ነባር ፕሮጀክት የአው አባድር አለም አቀፍ ስቴዲየም ግንባታ 92 በመቶ መጠናቀቁ የተገለፀ ሲሆን ግንባታውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ላለማጠናቀቅ ዋነኛው ምክንያት የስራ ተቋራጩ አቅም ማነስና ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ ሲስተዋል የነበረ ችግር እንደነበረም ተገልጿል ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ መረባረብ ይገባል።

ከፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን መቅረፍ አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ አመራሮች ተጠያቂ እንደሚሆኑ አመላክተዋል፡፡

የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ማከናወን የአዳዲስ ፕሮጀክቶችን ዝግጅት ምዕራፍ በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከግንባታ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የጨረታና የዲዛይን ችግሮች በፍጥነት ተቀርፈው ወደ ስራ እንዲገቡም እቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የካቢኔ አባላቱም በቀረበው ሪፖርት መነሻ በማድረግ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በማንሳት ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.