Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ያለውን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ ተጠቅሞ የሌማት ትሩፋት ዕቅድን ማሳካት ይገባል – ኢ/ር አይሻ መሃመድ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ ተጠቅሞ የሌማት ትሩፋት ዕቅድን ማሳካት ይገባል ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢ/ር አይሻ መሃመድ ገለጹ፡፡

ኢንጂነር አይሻ መሃመድ፣ ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን እና የተለያዩ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

ከጉብኝቱ በኋላም የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሃሊፋ ፥ የሌማት ትሩፋት የ6 ወራት አፈፃጸም ሪፖርትና የቀጣይ ጊዜያት ዕቅድ አቅርበው የጋራ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

አቶ አሻደሊ ሀሰን÷ ክልሉ ለእንስሳት እርባታ እና አሳ ሃብት ስራ ምቹ አካባቢ መሆኑንና ዘርፉን በማዘመንና የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማራባት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሌማት ትሩፋት ፕሮግራም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተጀመሩ ስራዎችን በቀጣይነት አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ዕቅዶችን ለማሳካት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና አጋር አካላት እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢንጂነር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው÷ የጉብኝቱ ዋና ዓላማ የሌማት ቱርፋቱ ያለበትን ደረጃ ተዘዋውሮ ለመመልከት እና በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች ግብዓት ለመሰብሰብ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በክልሉ የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም መግለጻቸውንም ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.