Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ የተሰረቁ ንብረቶችና ከ400 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ በርካታ የተሰረቁ ንብረቶችና ከ400 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ፖሊስ በከተማዋ የሚስተዋሉ የወንጀል ስጋቶችን ለመቀነስ ልዩ ዕቅድ አውጥቶ በትኩረት እየሰራ መሆኑን በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ም/ኮሚሽነር ሐሰን ነጋሽ ተናግረዋል፡፡

ከህብረተሰቡ በተገኙ ጥቆማዎችና ፖሊስ ባደረገው ጥናት መነሻነት ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ወንጀሎችን በመለየትና ወንጀሎች የሚፈፀሙባቸው አካባቢዎች ላይ የሰው ሃይል ጥበቃ በማድረግ የመከላከል ተግባራትን ከማከናወን ባሻገር የዘመቻ ስራዎችን በመስራት ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ አስረድተዋል።

በቀጥታ ወንጀሉን ከሚፈፅሙት ተጠርጣሪዎች ባሻገር በዘረፋና በስርቆት የተገኙ ንብረቶችን የሚቀበሉትን ግለሰቦች በጥናት በመለየት በእነሱ ላይ ተጨማሪ የዘመቻ ስራው መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ልዩ ዕቅድ በተሰሩ ስራዎች ለወንጀል መፈፀሚያነት ሲውሉ የነበሩና የተሰረቁ ተሽከርካሪዎች፣ በርካታ የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የግንባታ ዕቃዎች፣ የመሰረተ ልማት ግብዓቶች ፣ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና ሌሎች ንብረቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል፡፡

ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ የልዩ ዕቅድ ትግበራው እየተፈፀመና በእስካሁኑ ሒደትም 438 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

ወንጀል በከተማችን ላይ ስጋት የማይሆንበትን ሁኔታ በዘላቂነት ማረጋገጥ እንዲቻል የልዩ ዕቅድ ኦፕሬሽን ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን በተገኘው ውጤት ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና በማቅረብ ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.