Fana: At a Speed of Life!

የጨፌ ኦሮሚያ አራተኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጨፌ ኦሮሚያ ስድስተኛ የስራ ዘመን ሁለተኛ ዓመት አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል።

የክልሉ የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ለጨፌው የቀረበ ሲሆን፥ በክልሉ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር በተሰራው ሰፊ ስራ ለ1 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናግረዋል።

ክልሉ የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ ለመጠቀም በተደረገው ጥረት በበጀት አመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 78 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወስጥ ባለፉት ስድስት ወራት 38 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ተሰብስቧል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል በክልሉ የትምህርት ጥራት እና የተማሪዎች ውጤት አሳሳቢ በመሆኑ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የጨፌው አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረህማን በበኩላቸው÷ በክልሉ በረሃማ አካባቢዎች ያጋጠመውን ድርቅ ተከትሎ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ድርቁ አሁንም በመቀጠሉ ህብረተሰቡ፣ባለሀብቶች እና በተለይም የጨፌው አባላት በድርቁ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ ከተሰሩ የልማት ስራዎች ጋር በተያያዘ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት አፈጉባኤዋ በበጋው በስንዴ ልማት የተገኘው ውጤት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

ስንዴ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ መላኩ ትልቅ ስኬት እንደሆነም ነው አፈ ጉባኤዋ ያነሱት።

የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ የተመለከተ ሪፖርት እንደሚቀርብ የሚጠበቅ ሲሆን÷ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች እና ሹመቶች እንደሚፀድቁም ነው የተገለጸው፡፡

የክልሉ መንግስት አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ጠንካራ የጸጥታ ሀይል በመገንባት እየሰራ እንደሆነ አፈጉባኤዋ ገልፀው በክልሉ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው አሸባሪው ሸኔ በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ እንዲፈታም ጠይቀዋል።

የጨፌው ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡

በአዳነች አበበ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.