Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ከድርቅ ጋር በተያያዘ 3 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚሹ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ከድርቅ ጋር በተያያዘ 3 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚሹ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ገለጹ፡፡

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት አባላት ሰሞኑን በጋሞ፣ በጎፋ፣ በደቡብ ኦሞ እና በኮንሶ ዞኖች ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመስክ ምልከታ በማድረግ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ እርስቱ ይርዳው÷ ከዚህ ቀደም በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ድጋፍ ሲደረግላቸው ከነበሩ 917 ሺህ በላይ ዜጎች በተጨማሪ ወደ 2 ሚሊየን የሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚፈልጉ ነው የጠቆሙት።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ከተከሰተው ድርቅ ጋር በተያያዘ ወደ 1 ሚሊየን የሚጠጉ የቤት እንስሳትም ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማንሳታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የክልሉ አደጋ ስጋት ምክር ቤት ከተፈጠረው ድርቅ ጋር በተያያዘ ሰብዓዊ ጉዳት እንዳይደርስ እየሰራ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም እየተደረገ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት በዚህ ዓመት ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች 1 ሚሊየን ብር መድቦ እየሰራ መሆኑን ተናግረው ተጨማሪ በጀት በማፈላለግ የሰብአዊ ድጋፍ ስራውን ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች እየተካሔደ ያለውን የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ማጠናከር የጤና፣የንጹህ መጠጥ ውሃ፣የእንስሳት መኖ እና ተዛማጅ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.