Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነች ያለው ሥራ የሚደነቅ ነው-የፋዖ ዋና ዳይሬክተር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነች ያለው ሥራ የሚደነቅ መሆኑን የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶንግዩ ቹ ገለጹ።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶንግዩ ቹ ጋር ተወያይተዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ በውይይቱ÷ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት በአነስተኛ እና መካከለኛ መስኖ ዘርፍ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው እነዚህ የመስኖ አውታሮችን የበለጠ ለማጠናከር እየሠራን ነው ብለዋል።

በቀጣይ ያለውን የውኃ አቅም በመጠቀም በመስኖ ልማት፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎች ከድርጅቱ የ87 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ለፊርማ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

አረንጓዴ ልማቱ ከዛፍ በላይ ማድረግ ያሻል ያሉት ሚኒስትሩ ማኅበረሰቡ ገቢ እንዲያገኝባቸው የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

አንበጣን በመከላከል ረገድ ለኬሚካል መርጫ አውሮፕላን፣ ተሽከርካሪዎች እና ሌሎች ሎጂስቲክሶች አቅርቦት 1 ቢሊየን ብር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ድርጅቱ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶንግዩ ቹ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነች ያሉ ሥራዎችን አድንቀው ለአረንጓዴ ፓርክ ልማት ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ ከዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ጋር የረዥም ጊዜ ግንኙነት እንዳላት ጠቁመው በምግብ ራስን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት እና ስንዴ ውጪ መላክ መጀመሯንም ዋና ዳይሬክተሩ አድንቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.