Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የዜጎችን መፃኢ ዕድል ለመወሰን መሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል – አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የዜጎችን መፃኢ ዕድል ለመወሰን መሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ የኢፌዴሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና እና የምጣኔ-ሀብት ዕድል በር ለከፈቱ ግለሰቦች እና ተቋማት የሚሰጠው “የአፍሪካ የምግብ ሽልማት” አዲስ ሊቀ-መንበር ሾሟል።

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የሽልማቱ ኮሚቴ የቀድሞ ሊቀ-መንበር ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ለአዲሱ “የአፍሪካ የምግብ ሽልማት” ሊቀመንበር የቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጃካያ ሚሪሾ ኪኪዌቴ ኃላፊነቱን አስረክበዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የግብርና ሽግግር ቀጣይነት ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአፍሪካ አንገብጋቢ የሆነውን የምግብ ዋስትናን እና የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ለነገ የማይባል ሥራ መሆኑን በመግለጽ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ሀገራት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በተለይ በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የዜጎችን መፃኢ ዕድል ለመወሰን መሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የሽልማቱ ኮሚቴ የቀድሞ ሊቀ-መንበር ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በበኩላቸው፥ ሽልማቱ የአፍሪካን ግብርና ለማዘመን እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።

ሽልማቱ በአህጉሪቱ በግብርና እና ምግብ ዋስትና አስተዋፅኦ ላደረጉ ግለሰቦች እና ተቋማት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ እና ልምድ ልውውጥ ለአህጉሪቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።

አዲሱ “የአፍሪካ የምግብ ሽልማት” ሊቀመንበር የቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጃካያ ሚሪሾ፣ በተሰጣቸው ኃላፊነት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ የአፍሪካን ግብርና እና የምግብ ዋስትና ለማሻሻል እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የአፍሪካ የምግብ ሽልማትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል።

በአፍሪካ የምግብ ሽልማት ውስጥ ካሉት ኮሚቴዎች መካከል የቀድሞ የኢሴክስ መሥራች ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን ይገኙበታል።

“የአፍሪካ የምግብ ሽልማት” የአፍሪካን ግብርና ለሚያሸጋግሩ ግለሰቦች እና ተቋማት 100 ሺህ ዶላር የሚሸልም መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.