Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚለው መርህ ትቀጥላለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚለው መርህ እንደምትቀጥል ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም አፍሪካውያን አባቶች ችግሮችን ለመፍታት ይጠቀሙባቸው የነበሩ እውቀቶችን እንተገብራለን ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወደፊት በአፍሪካ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ተፈጥሯዊ እንደሆኑና መፍትሄው ከውስጥ መሆን አለበት ማለታቸውን በንግግራቸው አንስተዋል።

አፍሪካውያንም ልዩነቶቻቸውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት መፍታት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በንግግራቸውም ኢትዮጵያ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን መርህ እንደምተከል ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን በመሳሰሉ ሀገራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን ተሳትፎ እና ከኤርትራ ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ይህን መርህ በግጭት ወቅት መተግበሯንም ነው ያነሱት።

ከምግብ ሰብል ጋር በተያያዘ በምግብ ራስን መቻል ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፥ ኢትዮጵያ ባለፉት አራት አመታት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ መስራቷን አንስተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በአነስተኛ ግብርና የተሰማሩ አርሶ አደሮችን በክላስተር እና በሜካናይዜሽን እንዲያርሱ የሚያስችል ስራ መሰራቱንም ነው የጠቀሱት።

ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ የግብርና ምርቷን ወደ ውጭ ለመላክ የያዘችውን እቅድ እውን ማድረጓንም ነው የተናገሩት።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘም አፍሪካ ለአየር ንብረት መበከል አስተዋጽኦዋ አነስተኛ ቢሆንም እየተጎዳች መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህን ለመቅረፍ አፍሪካውያን መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

ከዚህ አንጻር ንግግሮች ወደ ተግባር ሊቀየሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ባለፉት አራት አመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 25 ቢሊየን ችግኞች መትከሏን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች እየተገበረች መሆኗንም በንግግራቸው ጠቁመዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም እንደ ቴሌኮም ያሉ ዘርፎችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት በማድረግ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ሀገር በቀል ማሻሻያ መተግበሩን አውስተዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.