Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ የተመጣጠነ ምግብ እጦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራት ለግብርና ፖሊሲያቸው ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል- ፋኦ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ እያጋጠመ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራት ለግብርና ፖሊሲያቸው ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ጥሪ አቀረበ።

በፋኦ እና በሌሴቶ መንግሥት አዘጋጅነት በአፍሪካ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግርን ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶችና ውጤቶች ላይ ያተኮረ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ተሳትፈዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግሮችን ለመቅረፍ ብሔራዊ ስትራቴጂ ቀርፃ እየተገበረች መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በተመጣጠነ ምግብ እጦት ሳቢያ የሚከሰተውን የህፃናት መቀንጨር ችግር በ2030 ለማጥፋት፤ ከአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር 2015 ጀምሮ የሰቆጣ ቃል-ኪዳን ስትራቴጂ ሰነድ ቀርፃ እየተገበረች መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአውሮፓውያኑ 2021 የሰቆጣ ቃል-ኪዳን ተደራሽነትን በማስፋፋት እስካሁን 3 በመቶ መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በወተት፣ በሥጋ፣ በእንቁላልና በከተማ ግብርና ምርቶችን ምርትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የሌማት ቱርፋት የተሰኘ መርሐ ግብር በይፋ ማስጀመሯን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ እንደ አህጉርና እንደ ዓለም የምግብና የተመጣጠነ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከልማት አጋሮቿ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

አጋር የልማት ድርጅቶችም የሰቆጣ ቃል-ኪዳን ፕሮግራምን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ፋኦ ዋና ዳይሬክተር ቹ ዶንግዩ እንደገለጹት÷ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ በተባባሰው የተመጣጠነ ምግብ እጦት ችግር ለተጎዱ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል።

የተሻሉ ተሞክሮዎችን ማስፋት በአፍሪካ ሕብረት በኩልም ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሀገራት በፓን-አፍሪካ መንፈስ የተመጣጠነ ምግብ እጦትን ችግር ለመፍታት የመንግሥታት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአፍሪካ በ100 ሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች በተመጣጠነ ምግብ እጦት ሳቢያ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸው፤ ሀገራት የግብርና ፖሊሲያቸውን ሲቀርጹ ከተመጣጠነ ምግብ ዋስትና አንጻር መቃኘት እንደሚገባቸው አመላተክዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.