Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬም እንደቀጠለ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ማፋጠን” በሚል መሪ ሐሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

ትናንት በተካሄደው ጉባዔ ኮሞሮስ የ2023 የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነትን ከሴኔጋል በይፋ የተረከበች ሲሆን ፥ የወቅቱ የሕብረቱ ሊቀ መንበር ሴኔጋል ለኮሞሮስ ሊቀ መንበርነቷን በይፋ አስረክባለች።

የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ በ2023 የአፍሪካ ሕብረትን በሊቀ መንበርነት እንደሚመሩም ነው የተገለጸው፡፡

በዚህ ወቅት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራትን ማዕከል ያደረገና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እንዲሆን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ላይ የተደቀኑ ችግሮችንና ይዘዋቸው ሊመጡ የሚችሉ ፈተናዎችን ቀድመን በመገንዘብ በጋራ ልናልፋቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡

የዋጋ ግሽበቱ ከሚጠበቀው በላይ ማሻቀብ፣ የነዳጅ ዋጋ መጨመርና ግጭት የአህጉሪቱ ተግዳሮቶች ሆነው መቀጠላቸውንም ግልጸው ፥ አማራጭ የመፍትሄ እርምጃ ማስቀመጥ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት እውን ለማድረግ ለንግድ ስራዎች በሚደረግ ጥበቃ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጣና እውን ለማድረግ መሰረተ ልማት፣ ኢነርጂኒና ዲጂታላይዜሽንን ማፋጠን የሚገባ ሲሆን ፥ ይህ ደግሞ ለነጻ ንግድ ቀጣናው እውን መሆን ዋነኛው መሰረት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በአህጉሪቱ የሚታዩ የፖለቲካና የደህንነት ችግሮች አሁንም ፈተና ሆነው መቀጠላቸውን በመጥቀስ ህገ መንግስታዊ ስርዓት በጣሰ መልኩ የሚደረጉ የመንግስታት ለውጦች ሀገራትን የመበታተን አደጋ እንደደቀነባቸው አመላክተዋል፡፡

ሽብርተኝነትና ከምርጫ ውጭ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ጥረትና የአየር ጸባይ ለውጥ አሁንም የአህጉሪቱ ችግሮች ሆነው መቀጠላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ሊቀመንበሩ በኢትዮጵያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት እውን እንዲሆን ጥረት ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጉባዔው ላይ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ እንዳሉት ፥ አፍሪካውያን አባቶች ችግሮችን ለመፍታት ይጠቀሙባቸው የነበሩ እውቀቶችን እንተገብራለን ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ፥ ኢትዮጵያ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን መርህ እንደምተከል አንስተዋል፡፡

በሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን በመሳሰሉ ሀገራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ኢትዮጵያ ያላትን ተሳትፎ እና ከኤርትራ ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ይህን መርህ በግጭት ወቅት መተግበሯንም ነው ያነሱት።

ከምግብ ሰብል ጋር በተያያዘ በምግብ ራስን መቻል ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፥ ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ መስራቷንም ነው ያነሱት።

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.