Fana: At a Speed of Life!

ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ከ17 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሰባት ወራት ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ከ17 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
 
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ጥናት መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎች ቁጥር ከ66 ሺህ በላይ ይሆናል።
 
ኑሮን መደጎሚያ ገንዘብ ማጣት፣ ድህነትና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ከተማ ለመፍለሳቸው መንስኤ ሲሆን÷ የወላጅ ማጣት፣ የአቻ ተፅዕኖና በወላጅ የሚደርስ ጥቃት ተጠቃሽ ምክንያቶች እንደሆኑም ጠቁሟል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሐና የሺንጉስ እንዳሉት÷ ውሎ እና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ለመመለስ ሥራዎች ቢሰሩም ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም።
 
ባለፈው ዓመት ብቻ መስተዳድሩ 79 ሚሊየን ብር በመመደብ ከ27 ሺህ በላይ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን የማቋቋም ሥራ መሥራቱን አስታውሰዋል።
 
93 በመቶዎቹ የከተማ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከክልሎች የፈለሱ እንደሆነ ገልጸው÷ ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ከ17 ሺህ 700 በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ ቀያቸው መመለስ መቻሉን ተናግረዋል።
 
ዜጎችን ከጎዳና ሕይወት የማንሳት ጥረቶች በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰው÷ ከተማ አስተዳደሩ ከክልሎች ጋር በመተባበር ችግሩን በጋራ ለመቅረፍ አስቻይ ተግባራትን ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
 
በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ በበጎ ፈቃድ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችም ሕይወታቸውን በጎዳና ላይ የሚመሩ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራዎችን በክልሎች ላይም ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
 
ዜጎች ወደ ጎዳና ከመውጣታቸው በፊት ከምንጩ ችግሮች እንዲቀረፉ ማገዝ ይገባቸዋል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.