Fana: At a Speed of Life!

ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች፡፡

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ዩን ሶክ ዮል ልዩ መልዕክተኛ እና ከፍተኛ የሥትራቴጂክ አማካሪ ጃንግ ሱንግ ሚን በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ጃንግ ሱንግ ሚን የስራ ጉብኝታቸውን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ÷ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ ታሪካዊ እና ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ በኮሪያ ጦርነት ወቅት ለደቡብ ኮሪያ ያደረገችው እገዛ ሁል ጊዜም የሚወሳ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ ለኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እያደረገች መሆኑን የገለጹት ልዩ መልዕክተኛው÷ በቀጣይም ትብብሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ደቡብ ኮሪያ ለአፍሪካ 500 ሚሊየን ዶላር እርዳታ ማድረጓን ጠቁመው÷ ከዚህ ውስጥም 20 በመቶው ወይም 100 ሚሊየን ዶላሩ ለኢትዮጵያ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ደቡቡ ኮሪያ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ልማት እና ሰላም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም ጃንግ ሱንግ ሚን አረጋግጠዋል፡፡

የሀገራቱን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርም በባህል እና ሌሎች ዘርፎች ላይ በቅንጅት እንደሚሰራ ነው የተናገሩት፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.