Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አራተኛ ዙር ሥልጠና ነገ ይጀመራል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አራተኛ ዙር ሥልጠና ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ አምሥት ቀናት እንደሚሰጥ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና በዓለም ባንክ ትብብር የአነስተኛ እና መካከለኛ አንቀሳቃሾች አራተኛ ዙር ሥልጠናን አስመልክቶ ባንኩ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ሥልጠናው በሀገር አቀፍ ደረጃ በ56 ከተሞች በተዘጋጁ 95 የሥልጠና ማዕከላት እና በ200 አሠልጣኞች እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአራተኛው ዙር የሥልጠና መርሐ ግብር 50 ሺህ ያህል ሰዎችን ሊያሰለጥን አቅዶ ለ14 ቀናት ባደረገው ምዝገባ 450 ሺህ ሰዎች መመዝገባቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሚሰጠው አራተኛ ዙር ስልጠና የተመዝጋቢው ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሥልጠናውን በሦስት ዙር እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

በነገው ዕለትም የመጀመሪያው ዙር ሥልጠና በሁሉም የሥልጠና ማዕከላት ለ112 ሺህ ሠልጣኞች የሚሰጥ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሃንስ አያሌው ገልጸዋል፡፡

የነገው የመክፈቻ ስነ ስርዓትም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ÷ ቀሪዎቹ ሁለት ዙሮች በሚቀጥሉት ጊዜያት ይሰጣሉ ብለዋል።

በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የሚገኙ የሥልጠና ማዕከላትም ሥልጠናውን በኢንተርኔት እንደሚከታተሉ ተናግረዋል፡፡
ባንኩ ለቅድመ ሥራ ማስጀመሪያ በ20 በመቶ ቁጠባ ዝቅተኛ የግዢ መጠን አምስት አክሲዮን በ5 ሺህብር በመግዛት መበደር የሚቻልበት ሁኔታ ማመቻቸቱ ተገልጿል።

በመራዖል ከድር

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.