Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ የዓየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የምታደርገውን ጥረት ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በገንዘብ ሊደግፍ ይገባል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አፍሪካ የዓየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የምታደርገውን ጥረት ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በገንዘብ እንዲደግፉ ጥሪ አቀረቡ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ÷ መልዕክታቸውን ለሚመለከታቸው ዓለምአቀፍ ተዋንያን ያስተላለፉት በአዲስ አበባ በተካሄደው የ2023 የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ላይ ነው፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ÷ ፎረሙ ለአፍሪካ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ርዕሠ-ጉዳዮች ለሚመለከታቸው ዓለምአቀፍ ተዋንያን እንዲደርስ ለማሠማት ጠቅሞናል ነው ያሉት፡፡

“ምንም እንኳን አፍሪካ በዓየር ንብረት ላውጥ ላይ ያላት ድርሻ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ገፈቱን ግን ከሌሎች አኅጉራት በላቀ መልኩ እየተጋተች ነው” ሲሉም የሁኔታውን አሳሳቢነት አንስተዋል፡፡

አፍሪካ የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ የምትችልበትን አዳዲስ ዘዴዎች መቀየስ እንደሚገባትና የአፍሪካ ሀገራት ታዳሽ የኃይል አማራጭ ለማበልፀግ አቅደው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የካርበን ሽያጭ ገቢ ÷ የአፍሪካ ሀገራት ታዳሽ የኃይል አማራጭ ላይ ለመሥራት እና በዓየር ንብረት ለውጥ የሚያደርስባቸውን ተፅዕኖ ለመከላከል አወንታዊ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት የልማት ዕቅድ የአፍሪካ ኅብረት በዓየር ንብረት ለውጥ ላይ እስከ ፈረንጆቹ 2063 ከያዘው እና ከ2030ው የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር ጎን ለጎን ሊሄድ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ10 ዓመታት የልማት ዕቅዷ ለዓየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሠራች መሆኗንም በፎረሙ ላይ አስረድተዋል።

አሁን ላይም ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንን ለመቀነስ የዓለም የሙቀት መጠን ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴሊሺየስ በላይ እንዳይጨምር ከተደረሰው የፓሪሱ የዓየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ጋር በተጣጣመ መልኩ እየሰራች መሆኑንም ነው የገለጹት።

እስከ 2050 ኢትዮጵያን ከካርበን ልቀት-ነፃ የሆነች ሀገር ለማድረግ የረጅም ጊዜ ዕቅድ እንደተያዘም አመላክተዋል፡፡

ለዚህም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከፍተኛው ሚና ይኖረዋልም ሲሉ ነው አቶ ደመቀ ያከሉት፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የግሉ ዘርፍ በሀገራዊ የታዳሽ ኃይል መስክ እንዲሳተፍ እንደሚያበረታታም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴው የኃይል አማራጭ ለመሻገር እና በዓለምአቀፍ ደረጃ በ2030 የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በምታደርገው ጥረት ከውኃ ፣ ከእንፋሎት ፣ ከነፋስ እና ከፀሐይ የሚገኙ የኃይል አማራጮችን ለማበልፀግ እየሠራች መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በታዳሽ የኃይል አማራጭ ላይ መዋዕለ-ንዋይ ማፍሠሥ ለሚፈልጉ ባለሐብቶችም አስፈላጊው አገልግሎት እና ማበረታቻ እንደሚቀርብላቸው አመላክተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.