Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በ10 ዓመት የመንገድ ሽፋኑን ከ51 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ለማድረስ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት በክልሉ ያለውን የመንገድ ሽፋን 51 ሺህ 565 ኪሎ ሜትር ለማድረስ እየተሠራ ነው አለ።

የቢሮው ኃላፊ ሙሐመድ ያሲን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ አሁን ላይ የክልሉ የመንገድ ሽፋን 29 ሺህ 478 ኪሎ ሜትር ነው፡፡

በያዝነው በጀት ዓመት ከ582 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ በመገንባት የክልሉን የመንገድ ሽፋን ከ30 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ለማድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣዮቹ 10 ዓመታትም ሽፋኑን 51 ሺህ 565 ኪሎ ሜትር ለማድረስ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡

በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት ከ112 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ መገንባቱን አቶ ሙሐመድ አንስተዋል፡፡

በመንገድ ጥገና ረገድም ከ3 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ታቅዶ 7 ሺህ 406 ኪሎ ሜትር በመጠገን የተሻለ አፈጻጸም ታይቷል ነው ያሉት፡፡

ለመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራው ከ752 ሚሊየን 277 ሺህ በላይ ብር ወጪ ሆኗል ብለዋል፡፡

በኪራይ የሚቀርቡ ማሽነሪዎች በሚፈለገው መጠን በገበያ ላይ አለመገኘት፣ የተቋራጮች የፋይናንስ አቅም ማነስ እና በወቅቱ ወደ ሥራ አለመግባት በሥድስት ወሩ ያጋጠመ ችግር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በፌደራል መንግሥት የሚሠሩ በተለይም በግጭቱ ምክንያት የቆሙ የአስፓልት ጅምር ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ አለመግባት በማህበረሰቡ ዘንድ ቅሬታ ማስነሳታቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.