Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠና ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አራተኛውን ዙር የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠና አስጀመረ።

በሚሊኒየም አዳራሽ 4 ሺህ ሰልጣኞች በተገኙበት በይፋ የተጀመረው ስልጠናው በመላ ሀገሪቱ በ57 ከተሞች በ95 ማዕከላት ለ112 ሺህ ሰልጣኞች ስልጠናውን ይወስዳሉ ተብሏል።

በስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሀት ካሚል እንዲሁም የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው ተገኝተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በእንደዚህ አይነት ስልጠና መታገዛቸው የኢኮኖሚ መሻሻል ለማምጣት ያስችላል።

በተለይም ኢትዮጵያ ለምታደርገው በምግብ ራስን የመቻል ጥረት መሠል ስለጠናዎች ሚናቸው ከፍተኛ ነው ፤ የሀገርንም ሆነ የመዲናዋን የልማት ዘርፍ ያሳድጋልም ነው ያሉት።

ሰልጣኞችም ስልጠናውን በንቃት እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው ÷ስልጠናው ከዓለም ባንክ ጋር በትብብር እንደሚሰጥ ገልፀው ፤ በዚህም ካለፉት ሦስት ዙሮች በበለጠ ከፍያለ ሰልጣኝ ስልጠና እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ባንኩ እስካሁን ባደረገው ስልጠና በድምሩ 33 ሺህ ሰልጣኞችን አብቅቶ በሊዝ ፋይናንስ 20 ቢሊየን ብር ጥቅም ላይ ማዋሉን ተናግረዋል።

በስልጠናው ከዚህ በፊት እድሉን ያላገኙ ጎዴና ጂንካ እንዲሁም የትግራይ ክልል ወጣቶች ተሳታፊ መሆናቸው ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

በዓለምሰገድ አሳዬና ሰለሞን ይታየው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.