Fana: At a Speed of Life!

የሊጉ ውድድር አመራርና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ የተለያዩ የሥነ ምግባር ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ የሥነ-ምግባር ግድፈት ባሳዩ የተለያዩ ቡድኖች እና ተጫዋቾች ላይ የሥነ ምግባር ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

በ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች አምስቱ በመሸናነፍ፣ ሶስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 23 ጎሎች በ21 ተጫዋች ተቆጥረዋል።

ጎሎቹም አንድ በፍፁም ቅጣት ምት ቀሪዎቹ በጨዋታ የተቆጠሩ ናቸው።

በሳምንቱ 19 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ፥ አንድ ተጫዋች ቀይ ካርድ መመልከቱን ከሊጉ ኮሚቴ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የሥነ ምግባር ሪፖርት መርምሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

የአዳማ ከተማው ተጫዋች ሚሊዮን ሰለሞን በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ በመወገዱ ለፈፀመው ጥፋት 1 ጨዋታ እንዲታገድ የተወሰነበት ሲሆን፥ የአርባምንጭ ከተማው ሱራፌል ዳንኤል በተለያዩ 5 ጨዋታዎች ቢጫ ካርድ በመመልከቱ አንድ ጨዋታ እንዲታገድና 1 ሺህ 500 ብር ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል።

አዳማ ከተማ የእግር ኳስ ቡድን ከኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረገው የ14 ኛ ሳምንት ጨዋታ አምስት ተጫዋቾቹ በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ 5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የክለቡ ደጋፊዎች የእለቱን ዳኛ አፀያፊ ስደብ በመሳደባቸው ክለቡ 50 ሺህ ብር እንዲቀጣ መወሰኑም ታውቋል።

የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ከወላይታ ዲቻ ጋር በነበረው የ14ኛ ሳምንት ጨዋታ የቡድኑ ተጫዋቾች 15 ደቂቃ ዘግይተው ወደሜዳ በመግባታቸው 25 ሺህ ብር እንዲከፍል እና የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት መብት ያለው ድርጅት የካሳ ክፍያ አክሲዮን ማህበሩን ከጠየቀ ክፍያውን ሙሉ በሙሉ ክለቡ እንዲሸፍን ውሳኔ ተላልፎበታል።

ኮሚቴው የለገጣፎ ለገዳዲ እግር ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ እና የቡድን መሪውን ለማነጋገር ጥሪ አስተላልፏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.