Fana: At a Speed of Life!

ከጉባዔው ጎን ለጎን ከአፍሪካውያን ጋር የበለጠ የሚያቀራርቡ ምክክሮች ተካሂደዋል- አምባሳደር ታዬ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ጎን ለጎን ከአፍሪካውያን ወንድሞች ጋር የበለጠ የሚያቀራርቡ ምክክሮች መካሄዳቸውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አማካሪ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አማካሪ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ የ36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን በተመለከተ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ እንደገለጹት÷ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከአፍሪካውያን ወንድሞች ጋር የበለጠ የሚያቀራርቡ ምክክሮች ተደርገዋል፡፡

ለአብነትም ከጉባዔው ቀደም ብሎ የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንት ኡማሮ ኢምባሎ ያደረጉትን ጉብኝ ጠቅሰዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ እየሠራቻቸው ያሉ ግዙፍ ልማቶችን መጎብኘታቸውን እና ለተቋማት ግንባታ መንግስት የሰጠውን ትኩረት መመልከታቸውን አምባሳደር ታዬ ገልፀዋል።

አፍሪካዊ ለሆኑ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በመስጠት ረገድ ኢትዮጵያ ሠርታ የማሳየት አብነት በመሆን እየተጓዘች ያለውን ርቀት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ማጉላታቸውን አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው÷ ጉባዔው የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ሁነኛ መድረክ ሆኖ ማለፉን ተናግረዋል፡፡

ጉባዔው በተሳትፎም ላቅ ያለ እንደነበር አስታውሰው÷ በስኬት የተጠናቀቀና ብሄራዊ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ ውይይቶች የተደረጉበት ነው ብለዋል፡፡

ኅብረቱ የሰላምና ደኅንነት ጉዳይን በተመለከተበት የኢትዮጵያን የሰላም ጉዞና በኅብረቱ ጥላ ስር መፍትሄ ለመስጠት የሄደበት ርቀት በአብነት መነሳቱንም ነው የገለጹት።

የኅብረቱን ሥራዎች ለማሳለጥ በተቋቋሙ የተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ የተሳትፎ እድል መገኘቱ ጥቅምን ለማስጠበቅ ለላቀ ሥራ የሚያነሳሳ መሆኑንም አንስተዋል።

በውይይቶቹ ኢትዮጵያ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ሰላሙን ለማፅናት እየሠራቻቸው ያሉ ሥራዎችን ለመግለፅ እድል የተገኘበት ነው ብለዋል አምባሳደር ምስጋኑ።

የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ ጉባዔው ከፀጥታ አንፃር ምንም አይነት የፀጥታ ችግር ሳይፈጠር የተጠናቀቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፀጥታ ግብረ ኃይሉ ከጉባዔው ቀድሞ እና በጉባዔው ወቅት የሠራቸው ሥራዎች እንዲሁም በሕዝቡ የተለመደ እና ቀና ተባባሪነት የጸጥታ ሥራው መሳካቱንም ነው ያነሱት፡፡

በሃብታሙ ተክለስላሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.