Fana: At a Speed of Life!

በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ከ263ሺህ በላይ ዜጎች እርዳታ እያገኙ አይደለም -ዞኑ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ263 ሺህ በላይ ዜጎች እርዳታ እያገኙ እንዳልሆነ የዞኑ አስተዳደር ገለፀ።

የዞኑ አስተዳዳሪ ጃርሶ ቦሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ በዞኑ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ከ867ሺህ በላይ ዜጎች ውስጥ 604 ሺህ ዜጎች እርዳታ እያገኙ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሆኖም ከ263 ሺህ በላይ የሚሆኑት እና አስቸኳይ እርዳታን የሚሹ ዜጎች ግን እርዳታ ያላገኙ ናቸው ብለዋል።

አሁን ላይ በድርቁ ምክንያት ከ378ሺህ በላይ የሚደርሱ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በ21 መጠለያ ጣቢያ ውስጥ እንደሚገኙም ተመላክቷል፡፡

ለእነዚህ ዜጎች እርዳታ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እና ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የጨመረ ቢሆንም ከተረጂ ቁጥር አንፃር እርዳታው አነስተኛ እንደሆነ አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

ለአንድ አባወራ 15ኪሎ ግራም እህል ብቻ የሚሰጥ መሆኑን የገለፁት አስተዳዳሪው ÷ በአንድ አባወራ ከ8 እስከ 10 ቤተሰብ ያለ በመሆኑ በቂ አይደለም ብለዋል።

ይህንንም ለማግኘት ተረጂው አንድ ወር መጠበቅ ግድ ይለዋል፤ይህም ሌላ ችግር ሆኗል ነው ያሉት።

ከምግብ እጥረት የተነሳ ህፃናትና አዛውንቶች ከፍተኛ ጉዳት ውስጥ እየገቡም መሆኑን የተገለፀ ሲሆን ÷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣውን ጉዳት ለመቀነስ ሁሉም እንዲረባረብ ዞኑ ጥሪ አቅርቧል።

በታሪኩ ለገሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.