Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ያለ ዕድሜ ጋብቻ ፈተና ሆኗል ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2015 (ኤፍቢ ሲ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በክልሉ በስፋት እየተፈፀመ ያለው ያለዕድሜ ጋብቻ ፈትኖኛል አለ።

በቢሮው የሴቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ስማቸው ዳኜ፥ ያለዕድሜ ጋብቻ በክልሉ በስፋት የሚፈፀም እና ክልሉን እየፈተነ ያለ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።

ለማግባት ከ18 ዓመት በላይ መሆንን ሕጉ ቢያስገድድም አሁን በክልሉ እስከ 16 ዓመት ያሉ ልጆች በተለያየ ምክንያት ጋብቻ እየፈፀሙ መሆኑን ጠቁመዋል።

በግማሽ ዓመቱ 86 ያለዕድሜ ጋብቻ መፈፀሙን ጥቆማ እንደደረሳቸው አቶ ስማቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

አሃዙ ወደ ቢሮ የመጡ ጥቆማዎችን እንደሚያሳይ ጠቅሰው ወደ ኅብረተሰቡ ቢገባ ሊጨምር እንደሚችል በመጥቀስ፥ ለዚህም ጋብቻ የሚፈፀመው በድብቅ መሆኑን በምክንያትነት ያነሳሉ።

ጥቆማዎቹ ተጨማሪ ማጣራት ተደርጎባቸው አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ለማስቻል ለሚመለከተው አካል መላካቸውንም ነው የሚናገሩት።

በሌላ በኩል በግጭቱ ምክንያት አስገድዶ መድፈር የተፈፀመባቸውን 3 ሺህ ገደማ ሴቶች መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ ነው ተብሏል።

ሥራው እየተከናወነ ያለው በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፥ በቢሮው እና በረጂ ድርጅቶች መሆኑም ተገልጿል።

በቋሚነት መልሶ የማቋቋም ሥራው የግለሰቦቹን ፍላጎት እና የአካባቢያቸውን ፀጋ መሰረት ባደረገ ጥናት ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በዚህም እንደየአካባቢያቸው በእንስሳት እርባታ እና ማድለብ እንዲሁም በንግድ ዘርፎች እየተሠማሩ ስለመሆኑም ያስረዳሉ።

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.