Fana: At a Speed of Life!

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 6ኛ ምርጫ 2ኛ የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በጋምቤላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
 
የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ትሁት ሃዋሪያት በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት÷ በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶች ከግብ እንዲደርሱ ሁሉም በአንድነት ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል።
 
በተለይም በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት የመስክ ምልከታ በማድረግ ደካማ ጎኖች እንዲታረሙና ጠንካራ ጎኖች እንዲጎለብቱ አቅጣጫ መቀመጡን አብራርተዋል።
 
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ባደረጋቸው የመስክ ምልከታና የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ ከተለዩት ቁልፍ ችግሮች መካከል በሆስፒታል እና በጤና ጣቢያዎች የመድኃኒት እና የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንደሚገኝበት አንስተዋል።
 
ከዚህ ባለፈም የግንባታዎች የጥራት ችግር እና በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቅ፣ የትምህርት ግብዓቶች አለመዳረስ፣ በጀትን ያላገናዘበ የባለሙያ ቅጥርና ምደባ እንደ ችግር መነሳቱን ወይዘሮ ትሁት ገልፀዋል።
 
የምክር ቤቱ አባላት የልማት ማነቆ የሆኑትን ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመታገል እንደ ሀገር የተጀመረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ዳር ለማድረስ በትጋት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
 
ለሶስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ የክልሉ አስፈፃሚ አካላት የ2015 የግማሽ በጀት ዓመት የልማትና መልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.