Fana: At a Speed of Life!

በሰሜን ኢትዮጵያ በ2ኛ ዙር 157 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብና ከ2 ቢሊየን ብር በላይ የሰብዓዊ እርዳታ ተሰራጭቷል

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ኢትዮጵያ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች በ2ኛው ዙር 157 ሺህ በላይ ሜትሪክ ቶን ምግብ መሰራጨቱን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በመላው ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ሳቢድጋፍ ለሚሹ 21 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች በዙር የእለት ምግብ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

ድጋፉም የሀገሪቱን አቅም ባገናዘበ መልኩ በመንግስት እና በተለያዩ አጋር አካላት የሚቀርብ መሆኑን ነው የገለጹት።

በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ በግጭቱ ሳቢያ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች በሁለተኛ ዙር የሚከናወነው የሰብዓዊ እርዳታ 92 በመቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ከታኅሣሥ ወር አጋማሽ እስከ የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በተከናወነ ስራም 157 ሺህ 852 ሜትሪክ ቶን ምግብ መሰራጨቱን አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም በትግራይ ክልል 1 ሚሊየን 316 ሺህ 848 ሊትር ነዳጅ እና 2 ቢሊየን 90 ሚሊየን 104 ሺህ 761 ብር ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ተደራሽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በርካታ የዕለት ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ የሚቀርበው የሰብዓዊ እርዳታ በቂ አለመሆኑም ተመላክቷል፡፡

ስለሆነም የግል እና መንግስታዊ ተቋማት እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.