Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስኬታማና ኢትዮጵያ አቅሟን ያሳየችበት ነው -አምባሳደር መለስ ዓለም

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስኬታማና ኢትዮጵያ አቅሟን ያሳየችበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለፁ፡፡

አምባሳደር መለስ ዓለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ እንዳሉት፥ በጉባኤው 29 የሀገራት መሪዎችና 53 የአፍሪካ ሀገራትና የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካና ሌሎች ሀገራት ተካፍለዋል፡፡

ጉባኤው የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችና በርካታ ሀገራት የተሳተፉበት መሆኑን በመጥቀስም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ጋር ተቀራራቢነት እንደነበረውም አውስተዋል፡፡

1 ሺህ የሚደርሱ ጋዜጠኞችም ሁነቱን እንደዘገቡት ቃልአቀባዩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ብሔራዊ ኮሚቴ በማቋቋም ጉባኤው ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ እንዲካሄድ ማድረጉንም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት።

ኢትዮጵያም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በንቃት በጉባኤው ተሳትፋለች ነው ያሉት።

ከጉባኤው ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ምስጋኑ አርጋ ከበርካታ የሀገራትና የተቋማት መሪዎች ጋር መወያየታቸውን አንስተዋል።

በግንኙነቶችም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ማስረዳት የተቻለበት፣ ድጋፎች ማግኘት የተቻለበት፣ የአዲስ አበባን የአፍሪካ መዲናነት ያፀና እንደሆነም ነው ያነሱት።

ጉባኤው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አንፃር ስኬታማና ግቡን የመታ ነበር ያሉት ቃል አቀባዩ ጉባኤውን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እንደተጠቀመችበትም ነው የሚናገሩት።

የአዲስ አበባ ህዝብም ለጉባኤው ስኬት ያበረከተው አስተዋፅኦ ጉልህ መሆኑን ተናረዋል።

ብዙ መሪዎችን በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ በማግኘት የኢትዮጵያን እውነት ማስረዳት መቻሉን፣ የሰላም ሁኔታውን ማስገንዘብ እንደተቻለ፣ የሰላም ስምምነቱ የተወደሰበት መሆኑን፣ ኢኮኖሚያ ፋይዳዎች መገኘታቸውንና የኢኮኖሚ መነቃቃት መታየቱን የጉባኤው ትሩፋቶች ብለዋቸዋል።

የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንት ኡማሮ ሲሳኮ ጉብኝትንም የበዛ ትርጉም ያለው ብለውታል።

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.