Fana: At a Speed of Life!

“ሜድ ኢን ጀርመን-አፍሪካ” የንግድ ዓውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ “ሜድ ኢን ጀርመን-አፍሪካ” የተሠኘ የንግድ ዓውደ-ርዕይ እንደምታስተናግድ ተገለጸ፡፡

የንግድ ዓውደ-ርዕዩ ከፈረንጆቹ መጋቢት 2 ቀን ጀምሮ እስከ 4 እንደሚቆይ ተመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ የምታስተናግደው ዓውደ-ርዕይ የአፍሪካ ሀገራትን ኢንዱስትሪዎች ከሌሎች ሀገራት የንግድ አጋሮች ጋር የሚያገናኝ ምኅዳር ለመፍጠር ያለመ መሆኑም መረጃውን ይፋ ያደረገው በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡

እንደ ኤምባሲው በኢትዮጵያ አዲስ አበባ በሚከፈተው ዓውደ-ርዕይ ላይ ከ2 ሺህ 500 በላይ የጀርመን እና የአፍሪካ የዘርፉ ባለሙያዎች ፣ ባለሐብቶች ፣ ዲፕሎማቶች እና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እንደሚካፈሉ እና በሚፈጥሯቸው ግንኙነቶች ሙያዊ ውይይት እንደሚያካሂዱ ይጠበቃል፡፡

የአፍሪካ እና የጀርመን ምሁራን በአኅጉሪቷ የትምህርት ዘርፍ እና ተቋማት ላይ ያሉ ችግሮችን ነቅሰው የመፍትሄ ሐሳብ ለማመላከት እንደሚመክሩም ተነግሯል፡፡

በተጨማሪ በመሠረተ-ልማት ዝርጋታ ፣ በዘመናዊ እና ንፁክ ከተሞች ግንባታ ፣ በሥነ-ኅንፃ በአካባቢ ጥበቃ ፣ በዲጂታል ዝርጋታ እና በማሽነሪዎች ምርት ላይ የተሰማሩ የጀርመን ኩባንያዎች በንግድ ትርዒቱ ላይ ከሚካፈሉት ሌሎች ተሳታፊዎች ጋር እንደሚገናኙና ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉም ተመላክቷል፡፡

ፕሮጀክቶችን በገንዘብ መደገፍ ፣ የግብርና ምርቶችን ለማቀነባበር የሚፈፀሙ የማሽን ግዢ ውሎች እና በሌሎች መሠል ጉዳዮች ላይም ሐሳብ ለመለዋወጥ የዓለም ባንክ ፣ አይ ኤም ኤፍ ፣ እና የጀርመኑ ኬ ኤፍ ደብል ዩ ባንኮች እንደሚሳተፉም ኤምባሲው ጠቁሟል፡፡

ዓውደ ርዕዩን የጀርመን ንግድ ሚኒስቴር እና የዓየር ንብረት ጥበቃ አዲስ አበባ ከሚገኘው ጀርመን ኤምባሲ እና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር እንደሚያዘጋጁት ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.