Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ሠራተኞች ወድቀው ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ የሕንጻው ግንባታ ፈቃድ ታገደ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ትናንት በግንባታ ላይ ከነበረ ሕንጻ ሦስት ሠራተኞች ወድቀው ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ዛሬ የሕንጻው የግንባታ ፈቃድ ታግዷል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በግንባታ ላይ ከነበረ ሕንጻ ላይ ሦስት የቀን ሠራተኞች ከአምስተኛ ወለል ወደታች ሲወርዱ የዕቃ መጫኛ ጋሪ ገመድ ተበጥሶ ወድቀው ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን የሕንጻውን የግንባታ ፈቃድ አግዷል፡፡

የሕንጻው ባለቤት እስከ አራተኛ ወለል የግንባታ ማስጀመሪያ ፈቃድ የተሰጣቸው ቢሆንም ግንባታውን ከጀመሩ በኋላ እስከ አምስተኛ ወለል ድረስ በማስቀጠል ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ ግንባታ ማከናወናቸውን የባለስልጣኑ የግንባታ ቁጥጥር ዳይሬክተር ከማል ጀማል ተናግረዋል፡፡

በሕንጻው ሠራተኞች ሲወጡና ሲወርዱ የደኅንነት ቀበቶ ባለመኖሩ እና ዕቃ ማውጫና ማውረጃው በአሮጌ ሽቦ የታሰረ በመሆኑ ምክንያት ሠራተኞቹ ከአምስተኛ ወለል ወደ ታች ሲወርዱ ተበጥሶ በመውደቃቸው ሕይወታቸው ማለፉን አስታውሰዋል፡፡

ቀደም ሲልም ለሕንጻው ባለቤት በቁጥጥር ባለሙያዎች አማካኝነት እንዲያስተካክሉ ቢነገራቸውም ይህን ባለመተግበራቸው የሰው ሕይወት ማለፉን አቶ ከማል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ በተመሳሳይ ተግባር ላይ የሚገኙ ሕንጻዎች ላይ የግንባታ ፈቃድ በማገድና በመሰረዝ እርምጃ እንደሚወሰድም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.