Fana: At a Speed of Life!

ባለሃብቶች በመዲናዋ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለሃብቶች በአዲስ አበባ ከተማ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በኮሚሽኑ የእቅድና በጀት ዳይሬክተር እናትነሽ ታመነ እንደገለጹት ÷ በመዲናዋ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው፡፡

በግማሽ ዓመቱ 3 ሺህ 150 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲወስዱ፣ እንዲያድሱ እና እንዲያሻሽሉ ለማድረግ ታቅዶ 2 ሺህ 863 ማከናወን መቻሉን አንስተዋል፡፡

በዚህም የእቅዱን 90 በመቶ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ጠቁመው÷ለ2 ሺህ 834 ዜጎችም ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለ424 ፕሮጀክቶች እና ወጪ ምርቶችን የሚያሳድጉና ገቢ ምርቶችን ለሚተኩ 15 ተቋማት ክትትል እና ድጋፍ መደረጉን ወ/ሮ እናትነሽ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

የኮሚሽኑ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ ÷ በዚህም ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለአልሚዎች አስፈላጊ ግብዓቶችን እና መሰረተ ልማቶችን ከማሟላት አንጻርም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትስስር እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በመዲናዋ አሁን ላይ ያለውን አስተማማኝ ጸጥታና የመሰረት ልማት ዝርጋታ ግምት ውስጥ በማስገባት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.