Fana: At a Speed of Life!

ታዋቂው ብስክሌተኛ ገረመው ደምቦባ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አንጋፋው እና ታዋቂው ብስክሌተኛ ገረመው ደምቦባ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

የብስክሌት ስፖርተኛው ገረመው ደንቦባ በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በትናንትናው ዕለት በ90 ዓመቱ ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል፡፡

ብስክሌተኛው ኢትዮጵያ በተሳተፈችበት ሜልቦርን ኦሊምፒክ በብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያን ወክሎ በመሳተፍ እና ሰንደቅ አላማዋን በኦሊምፒክ በመያዝ ቀዳሚው አትሌት ነበር።

ገረመው ደምቦባ ታህሳስ 7 ቀን 1925 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለደ ሲሆን እ.አ.አ በ1956 ዓ.ም ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት 16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በብስክሌት እና አትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል።

አንጋፋው ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ በፈረንጆቹ በ1973 በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው ሁለተኛ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የብስክሌት ቡድን ይዞ በመጓዝ ወርቅ ይዞ ተመልሷል።

ገረመው ደንቦባ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው የብስክሌት ተወዳዳሪዎች ሁሉ ስኬታማ እንደሆነ ይነገርለታል።

በተለያዩ ውድድሮች ተሳትፎ 26 ዋንጫዎች እና 32 ሜዳልያዎችን ተሸልሟል።

የታዋቂው እና የአንጋፋው ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ የቀብር ስነ-ስርዓት ነገ በብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ-ክርስቲያን ከቀኑ 8 ሰአት ላይ እንደሚፈጸም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.