Fana: At a Speed of Life!

በቦረና ለተጎጂዎች የሚቀርበው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦረና ዞን ለተጎጂዎች የሚቀርበው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ በሰው እና እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡

የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ ከ 3ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ እንስሳት በድርቁ መሞታቸውን የገለጸ ሲሆን ፥ በአሁኑ ወቅት  ለተጎጂዎች ዕርዳታዎች እየቀረቡ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ነው ያስታወቀው፡፡

ባለፉት 3 ዓመታት ዝናብ ባለመኖሩ ምክንያት ከ 800 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍል ለከፋ ችግር መጋለጡም ነው የተነገረው፡፡

የሚጠበቀው ዝናብ በወቅቱ ካልጣለ ችግሩ ከዚህ የከፋ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳለውም ዞኑ በሰጠው መግለጫ ገልጿል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በድቡልቅ የድርቅ ተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ ያገኛቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም በአካባቢው በተከሰተው አስከፊ ድርቅ የደረሰባቸውን ጉዳት መታዘብ ችሏል፡፡

በዞኑ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል አርብቶ አደር መሆኑና ከእንስሳት ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያለው በመሆኑ ድርቁ ባስከተለው ችግር ለከፋ ጉዳት መዳረጉን የገለጹት የቦረና ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ቦሩ ናቸው፡፡

የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ተቋም ምክትል ሀላፊ ዶ/ር መሊቻ ሎጂ እንዳሉት ፥ በቂ ባይሆንም እንኳን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የተወሰኑ እንስሳትን ለማዳን የእንስሳት መኖን እያቀረበ ነው፡፡

አቶ ጃርሶ ፥ ድርቁ አሁን ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት አንጻር ዕርዳታ እየቀረበ ቢሆንም ጉዳት ከደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥር አንጻር በቂ አለመሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በቦረና ዞን ብቻ በ3 ዙር ከ 375 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በፌዴራልና በክልሉ ቡሳ ጎኖፋ አማካኝነት የምግብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እየቀረበ ነው ያሉት ዶክተር መሊቻ ፥ የክልሉ የመንግስት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.