Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል 28 ትራክተሮች ለ13 ወረዳዎች እና ለጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ተከፋፈለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ 28 ትራክተሮች ለ13ቱ ወረዳዎች እና ለጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ርክክብ አካሄደ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት÷ የእርሻ ትራክተሮቹ በክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ መሳካት የጎላ ፋይዳ አላቸው ፡፡

በተጨማሪም አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮቹ በተደጋጋሚ ለሚያነሷቸው የእርሻ ትራክተር ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነ አስረድተዋል።

ትራክተሮቹ በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር እንደሚያግዙ ጠቁመው ሁሉም ወረዳዎች ትራክተሮቹ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

ትራክተሮቹ በየወረዳው የተደራጁ ሴቶችና ወጣቶች ካሉ ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ በበኩላቸው÷ዛሬ ለወረዳዎችና ለከተማ አስተዳደሩ የተከፋፈሉት የእርሻ ትራክተሮች ክልሉ ከድህነት ለመውጣት የሚያግዝ እንደሚሆን መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.