Fana: At a Speed of Life!

ደብረብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች አፋጣኝና የተደራጀ ድጋፍ ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ደብረብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች አፋጣኝና የተደራጀ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ገለፀ፡፡

ከዚህ ቀደም በከተማዋ 26 ሺህ ተፈናቃዮች በስድስት ማእከላት የነበሩ ሲሆን÷ አሁን ላይ በየቀኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ወደ ከተማዋ ተፈናቅለው እየመጡ መሆኑ ተመላክቷል።

በከተማ አስተዳደሩ የተቋቋመው የተፈናቃይ ኮሚቴ አባል አቶ ግርማ ድባቤ እንዳሉት÷ በየቀኑ የሚመጡ ተፈናቃዮች ቁጥር መጨመር ከከተማው አቅም በላይ በመሆኑ መጠለያና እርዳታ ለመስጠትም ችግር እያጋጠመ ነው።

ከሰሞኑ ብቻ ከ3 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ጠቅሰው፥ ግለሰቦችና ማህበረሰቡ በግል ተነሳሽነት ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ አፋጣኝ የተደራጀ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ወደ ደብረብርሀን ከተማ የመጡ ተፈናቃዮች “የህግ አግባብን በጣሰ መንገድ ከቤታችን ተፈናቅለናል” ሲሉ ተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰባቸው መቆየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት በመስጠት እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

በኤልያስ ሹምዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.