Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ከ245 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ።
ፕሮጀክቶችን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪንና የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በጋራ መርቀዋቸዋል።
በመንገድ ልማት ፕሮግራም የሸንኮር አስፋልት መንገድ፣ የእግረኛ መንገድና የመንገድ ዳር መብራት አካቶ መገንባቱ በስነስርዓቱ ተጠቁሟል።
የሁለተኛ ደረጃ ሞዴል ትምህርት ቤት፣ የወጣቶች ስብእና ልማት ማእከል እንዲሁ በማህበራዊ ልማት ፕሮግራም ታቅፈው ሲገነቡ ቆይተዋል።
በቤት ልማት ፕሮግራም የተገነቡት የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ፕሮጀክት፥ በክልሉ ለዘመናት የተሻገረውን የመምህራን የቤት ጥያቄዎች ለመመለስ ያስችላሉ ተብሏል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ፥ የፕሮጀክቶቹ በተቀናጀ ሁኔታ መገንባት የከተሞችን ሁለተናዊ እድገት ለማሳለጥ ይረዳል ብለዋል።
የክልሉ መንግስትም የነዋሪዎቹን የመሠረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተጓዘበት ያለውን ርቀት አድንቀዋል።
ይህም ገጠር ብቻ ሲለማ ከተማ ይለማል የሚለውን የተዛባ አስተሳሰብ የቀየረ ስራ መሆኑንም ነው ያነሱት።
በቀጣይም ከተማንና ገጠርን በራሳቸው አቅጣጫ እንዲለሙ እንደሚደረግ ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ሐረርን ለነዋሪዎቿ የተመቸች ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
የሸንኮር የተቀናጀ ልማት ኢኒሺየቲቭም የዚሁ አንድ አካል መሆኑን አመላክተዋል።
ፕሮጀክቱ በተቋማት ቅንጅትና የህብረተሰቡ አጋርነት የታየበት ስለነበረ በሁለት አመት ተኩል ባነሰ ጊዜ ተሰርቶ መጠናቀቁንም ነው የተናገሩት።
በኢዮናዳብ አንዱዓለም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.