Fana: At a Speed of Life!

ወደ ቱርክ የተጓዘው የኢትዮጵያ የፍለጋ እና ሕይወት አድን ቡድን ተልዕኮውን አጠናቆ ተመለሰ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ ቱርክ ደቡባዊ ክፍል ተጉዞ የነበረው የኢትዮጵያ የፍለጋ እና ሕይወት አድን ቡድን ተልዕኮውን አጠናቆ ተመለሰ።

በቅርቡ በቱርክ ደቡባዊ ክፍል የደረሰውን ርዕደ መሬትን ተከትሎ እስካሁን ከ47 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉ እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ካላት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተነሳ መንግስት በሰጠው ውሳኔ መሰረት ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አጋርነቷን በተግባር ለማሳየት የእርዳታ ቁሳቁስ የያዘ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ከጤና ሚኒስቴር የተውጣጣ 27 አባላት ያሉት የፍለጋ እና ሕይወት አድን ቡድን ወደ ስፍራው ማቅናቱ የሚታወስ ነው።

በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መሃንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ደስታ አብቼ የተመራው ልዑካን ቡድን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና በሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል ተደርጐለታል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ድጋፋ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ከማጠናከር ባለፈ የህዝቦችን የአለኝታነት ስሜት የሚፈጥር ነው ብለዋል::

አያይዘውም የኢትዮጵያ መንግስት ላደረገው ድጋፍ የልዑካን ቡድኑ አባላት የነፍስ አድን ስራ በመስራት ላይ እያሉ የቱርክ ፕሬዚዳንት ራሲፕ ጣይፕ ኤርዶኻን በቦታው ተገኝተው በቱርክ ህዝብና መንግስት ስም ምስጋና ማቅረባቸውን ገልፀዋል።

የልዑካን ቡድኑ በቱርክ በነበረው ቆይታ በድጋሜ የተከሰተውን የርዕደ መሬት አደጋ ተቋቁሞ ግዳጁን ፈፅሞ መመለሱ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ተቋም አኩሪ ተልዕኮ ነው ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.