Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ሩሲያ ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች እየተጠናከረ መጥቷል – አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ሩሲያ ያላቸው ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች እየተጠናከረ መምጣቱን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን ገለጹ።

የኢትዮጵያና ሩሲያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩበትን 127ኛ ዓመት በዓል በአዲስ አበባ ሩሲያ ኤምባሲ ተከብሯል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን እንደገለጹት÷ በአሁኑ ወቅት የሩሲያና ኢትዮጵያ ግንኙነት ጠንካራ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ትብብሩን የበለጠ ለማጠናከር በሁለቱ ሀገራት ከተሞች ሞስኮና አዲስ አበባ መካከል በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ የሚደረጉ ውይይቶችን ጠቅሰዋል።

በሁለቱ ሀገራት የፓርላማ ግንኙነትና በሰብዓዊ እርዳታ እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ነው ያነሱት።

የሁለቱ ሀገራት ትብብር በኢንዱስትሪ፣ በግብርና እና በኃይል ዘርፍም መጠናከሩን አንስተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳሬክተር ጀነራል አምባሳደር እሸቱ ጥላሁን በዚሁ ወቅት ÷ በተመድ የጸጥታው ም/ቤት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል በነበረው ስብሰባ ሩሲያ ለኢትዮጵያ ለሰጠችው ድጋፍ አመስግነዋል።

እንደ ኤውሮፓውያን አቆጣጠር በ1896 የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ኢትዮጵያን ለመውረር በመጣበት ጊዜ በአድዋ በተደረገው ተጋድሎ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟን አውስተዋል።

ሩሲያ በ1895 ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር በመጣችበት ወቅት 30 ሺህ ጠበንጃ 5 ሺህ ጎራዴዎችን ለኢትዮጵያ ወታደሮች መላኳን ጠቅሰዋል።

በነዚህና በሌሎች በተግባር የተደገፉ ግንኙነቶች ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ላላት የጠበቀ ግንኙነት ትልቅ ዋጋ እንደትሰጥ በአጽአኖት አንስተዋል።

ሁለቱ አገራት ያላቸውን የጠበቀና ታሪካዊ ግንኙነት በምጣኔ ሃብት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው÷ በትብብር ሊሰሩባቸው የሚችሉ በርካታ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዳሉ አመላክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.