Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋን ድል ለብሄራዊ መግባባትና ለመከላከያ ሠራዊት ግንባታ እንጠቀምበታለን- ጄ/ል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋን ድል ለብሄራዊ መግባባትና ለመከላከያ ሠራዊት ግንባታ እንጠቀምበታለን ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ።

የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት በ127ኛው የዓድዋ ድል በዓል አከባበር በማስመልከት ከሀገር ውስጥ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች እና የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ጄኔራል አበባው ባስተላለፉት መልዕክት÷ መከላከያ የዓድዋ በዓልን በሃላፊነት ወስዶ ደረጃውን በሚመጥን መልኩ እንዲከበር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድነት ሆነው የሰለጠነውን ወራሪ ሃይል ተዋግተው ያሸነፉበት ጦርነት ነው ያሉት ጄነራል መኮንኑ÷ የአያቶቻችን የውጊያ ስልት ፣የግንኙነት ስርዓት እና የጦር አመራር ስልት ልንማርበት ይገባል ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድል የአንድነት ተምስሌት በመሆኑ ለብሔራዊ መግባባት ለሠራዊት ግንባታና ለቱሪዝም በመጠቀም ገጽታችንን መገንባት ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ እና የመላው ጥቁር ህዝቦች የኩራት ምንጭ የሆነውን የዓድዋ ድል ታሪኩን በሚመጥን መልኩ ዘግቦ ለትውልድ ማሸጋገር ከእያንዳንዱ የሚድያ ተቋምና ባለሙያ የሚጠበቅ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

መከላከያ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በበኩላቸው÷ በዓሉን በተሳካ ሁኔታ ለማክበር ከመገናኛ ብዙኀን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ መናገራቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.