Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 7 ወራት ከ258 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል – የገቢዎች ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሰባት ወራት በገቢዎች ሚኒስቴር እና በጉምሩክ ኮሚሽን ከ258 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ አስታወቁ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን የሰባት ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና በቀሪ ወራት በትኩረት በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ ሲያካሂድ የቆየውን ውይይት ዛሬ አጠናቋል፡፡

በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ፥ የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን የተሰጣቸውን ተልእኮ በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሰባት ወራት የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን መግለጻቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት በመሰብሰብ እና የመንግስትን የልማት ወጪ ፋይናንስ ለማደረግ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሯ አክለዋል፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ ታክስ 266 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር እና ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ 183 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በድምሩ 450 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው ያስረዱት፡፡

ባለፉት ሰባት ወራትም 262 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ 258 ነጥብ 93 ቢሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን ፥ የእቅዱን 98ነጥብ 79 በመቶ ተሳክቷል፡፡

የጉምሩክ አገልግሎትን ዘመናዊና ቀልጣፈ ለማድረግ እስከዛሬ ተሰርተው ተግባራዊ ከተደረጉት የቴክኖሎጂ አማራጮች በተጨማሪ አገልግሎቱን ወረቀት አልባ በማድረግ ተወዳዳሪ ተቋም ለመገንባት እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

ባለፈው ሰባት ወር አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት ሚኒስትሯ ፥ በቀጣዩ አምስት ወር ካለፈው ሰባት ወር መልካሙን ወስደን ያየናቸውንና የገመገምናቸውን ክፍተቶች ሞልተን እንቀጥላለን ብለዋል።

በቀጣይም የሰው ሀይል ከማብቃት በተጨማሪም የስነምግባር ጉድለት ያለባቸውን ሰራተኞቹን እያረመ አሰራሩንም ዓለም በደረሰበት የቴክኖሎጂ ውጤት እየደገፈ እንደሚቀጥልም ነው ያነሱት።

በተጨማሪም በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመትም 40 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ መንግስት ሊያጣው የነበረን ገንዘብ ከህገወጦች ማዳን መቻሉን የገለጹት ደግሞ የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ናቸው ፡፡

ትናንት በተጀመረው የግምገማና ውይይት መድረክ በቀጣይ ወራት በትኩረት የሚሰሩ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ተቀምጦ መድረኩ ዛሬ ተጠናቋል።

በታምሩ ከፈለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.