Fana: At a Speed of Life!

ለመኸር ወቅት ማዳበሪያ ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እየተሰራጨ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ለ2015/2016 የመኸር ወቅት የሚውል ማዳበሪያ ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ዩኒየኖች እያሰራጩ ነው፡፡

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ መስፍን ረጋሳ እንደገለጹት፥ ለ2015/16 የመኸር ወቅት 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ተጠቅመን ከተረፈው ጋር ተደምሮ እስካሁን 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ወደ ዞኖች፣ ዩኒየኖች እና ኅብረት ሥራ ማኅበራት እየተጓጓዘ ነው ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ለ2015/2016 የመኸር ወቅት 9 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አጀበ ስንሻው ተናግረዋል፡፡

እስካሁን 927 ሺህ 875 ኩንታል ወደ ክልሉ መግባቱን እና 315 ሺህ 556 ኩንታል ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት መድረሱን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል 78 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ስለመዘጋጀቱም አመላክተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ ማቴዎስ አኒዮ፥ ለምርት ዘመኑ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

እስካሁንም 371 ሺህ 682 ኩንታል መቅረቡን እና 32 ሺህ 750 ኩንታሉ መሰራጨቱን አስረድተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት እና የገጠር ፋይናንስ ዳይሬክተር ተስዬ በቀለ፥ ወደ ክልሉ 85 ሺህ 729 ኩንታል ማዳበሪያ መግባቱን ነው የተናገሩት።

ከዚህ ውስጥም 62 ሺህ 90 ኩንታል ወደ ቀበሌዎች ተሰራጭቷል ነው ያሉት፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አስራት አሰፋ÷ 149 ሺህ 760 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ለማስገባት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ወደ ክልሉ ከገባው 70 ሺህ 185 ኩንታል÷ 8 ሺህ 195 ኩንታሉ ወደ ማኅበራት መድረሱን ነው ያስታወቁት።

ዘንድሮ ግብዓቱ ቀደም ብሎ መቅረቡ እና መሠራጨቱን ኃላፊዎቹ በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

ማዳበሪያው ወደ ክልሎቹ እና ወደ ማኅበራት የማሰራጨት ሥራው እየተከናወነ መሆኑንም ነው የሥራ ኃላፊዎቹ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/

ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

 

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.