Fana: At a Speed of Life!

በግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሀገር ውስጥ የስራ ስምሪት አገልግሎት መመሪያ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግል ስራ እና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሀገር ውስጥ የስራ ስምሪት አገልግሎት ስለሚሰጡበት ሁኔታ ለመወሰን በወጣው መመሪያ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በውይይቱ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ንጉሱ ጥላሁን እና ከተለያዩ  የኤጀንሲ ተወካዮች የተውጣጡ ባለ ድርሻ አካላት  ተሳትፈዋል።

በውይይቱ  አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት÷ የግሉ ዘርፍ ለስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የስራ ዕድል በቅጥርና በራስ  እንደሚፈጠር ጠቅሰው÷ መንግስት ለግሉ ዘርፍ የስራ ዕድል ፈጠራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሰሪና ሰራተኞች መብታቸው እንዲጠበቅና ግዴታቸውንም እንዲወጡ የሁለቱ ግንኙነቶች የተሳካ እንዲሆን ምቹ ሁኔታንም መፍጠር ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡

ሁኔታዎች ባልተመቻቹበት ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት አይቻልም ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው÷ የአሰሪና ሰራተኛው ጥቅሞቹ መብቱና ደህንነቱ ሊጠበቅለት ይገባዋል ብለዋል ።

ከአሰሪዎች ጋር በቅርበት መስራት ተጠቃሚነቱን ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸው÷ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍም የዛሬው ውይይት ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን አመላክተዋል።

ውይይቱ በቀጣይ የሀገር ውስጥ የስራ ስምሪቶች ላይ ምን መደረግ አለበት ከሚለው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከመግባባት ለመድረስ የሚደረግ ነውም ተብሏል፡፡

ያለውን የሥራ-አጥ ቁጥር ችግር ለመፍታትም ኤጀንሲዎችን ጭምር በማስተባበር እስከ 2017 ዓ/ም ለ14 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል።

የሥራ ዕድል ፈጠራው የድርጊት መርሐ- ግብር እስከ 2022 ዓ/ም ድረስ ቀጥሎ 20 ሚሊየን ዜጎችን የሥራ ባለቤት የሚያደርግ ነው ተብሏል።

የኢፌዴሪ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ በፈረንጆቹ 2021 ባደረገው የዳሰሳ ጥናት መሰረት በገጠርና በከተማ ያለው የሥራ-አጥ ቁጥር በአማካይ 8 በመቶ እንደሆነ በመድረኩ ተመላክቷል።

በይስማው አደራው እና መሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.