Fana: At a Speed of Life!

በቦረና ዞን ከ754 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦረና ዞን ከ754 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር አብዱል ካማራ እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ድጋፍ የሚገነባ መሆኑን አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ የአፍሪካ ልማት ባንክ በቦረና እና አካባቢው የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የሚያስችል የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታ የማስፋፊያ አቅድ አካል መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዙር ይፋ መሆኑን ጠቁመው ÷ በቀጣይ ዙር በ60 ሚሊየን ዶላር ለሚተገበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ስምምነት መፈጸሙንም ነው የተናገሩት።

በሁለተኛው ዙር ፕሮጀክት ሰባት ነባር የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶች እንደገና በአስቸኳይ ስራ እንዲጀምሩ እንደሚደረግ እና አምስት አዳዲስ ጥልቅ ጉድጓዶች እንደሚቆፈሩም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ምድረ ሜካኒካል እና ፓምፖች የሚገጠሙለት ከሶስት እስከ አራት የሚደርሱና 1 ሺህ ሜትር ኪዩብ የሚይዙ የውሃ ጋኖች፣ የቧንቧ መስመር ዝርጋታ እና ሌሎች ስራዎች እንደሚከናወኑም አስረድተዋል፡፡

የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ በቦረና አካባቢ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች ለማስረከብም ከሚመለከታቸው አካላ ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.