Fana: At a Speed of Life!

ወደ መቀሌ እና ሽረ በሚደረጉ በረራዎች ከታሪፍ በላይ በማስከፈል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ እና ሽረ በሚያደርጋቸው በረራዎች በአዲስ አበባ እና በመቀሌ ተመድበው የሚሠሩ አንዳንድ ባለሙያዎችና ከአየር መንገዱ ጋር የሚሠሩ ኤጀንቶች ጉዳይ እናስፈጽማለን ከሚሉ ግለሰቦች ጋር ተመሳጥረው ከተቀመጠው የክፍያ ታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ ስለተደረሰባቸው ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው÷ ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉና ኅብረተሰቡን ለእንግልት ሲዳርጉ የተደረሰባቸው በሙሉ ጉዳያቸው ተጣርቶ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ በጋራ እየተሠራ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በቀን ወደ መቀሌ የሚደረገው የበረራ ቁጥር ወደ አምስት ማደጉን እንዲሁም ወደ ሽረ የሚደረገው በረራም በሳምንት ወደ ዘጠኝ ከፍ ማለቱን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

አስፈላጊው የሰው ኃይል በየበረራ መዳረሻው ተመድቦ ደኅንነቱ በተረጋገጠ ሁኔታ ተጓዦች በቂ አገልግሎት እንዲያገኙ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ሆኖም በርካታ ሰዎች የአየር ትራንስፖርት የመጠቀም ፍላጎታቸው መጨመሩን እንደመልካም አጋጣሚ የወሰዱት በአዲስ አበባ እና በመቀሌ የተመደቡ ሙያዊ ሥነ-ምግባር የጎደላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንዳንድ ሠራተኞችና ከአየር መንገዱ ጋር የሚሠሩ ኤጀንቶች ከጥቅም ተጋሪ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ከተቀመጠው የክፍያ ታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ እንደነበር ተደርሶበታል ነው ያለው መግለጫው፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጉዳዩ ዙሪያ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው በድርጊቱ ሲሳተፉ የነበሩ አራት ግለሰቦች በመለየታቸው እጅ ከፍንጅ ተይዘው ጉዳያቸው መቀሌ ፖሊስ ጣቢያ በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኝ መግለጫው አስታውቋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሢሠሩ የነበሩ አምስት ኤጀንቶች ከሥራ ታግደው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ሌሎች በጉዳዩ የተሳተፉ አካላትን በመለየት እርምጃዎች ለመውሰድ መረጃዎችን የማጠናቀር ሥራ እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡

ኅብረተሰቡ በሕጋዊ አሠራር እና ይህንኑ ለማከናወን ከተደራጀ ቢሮ ብቻ ቀርቦ ትኬቱን በመቁረጥ በተቀመጠው የተቋሙ ታሪፍ ብቻ አገልግሎት ማግኘት የሚችል መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ባልተገባ መንገድ በሕገ-ወጦች ተታሎ እላፊ ገንዘብ እንዳይከፍልና እንዳይጭበረበር እንዲጠነቀቅ ተጠይቋል፡፡

ከዚህ ውጭ ኅብረተሰቡ በማንኛውም ሁኔታ ለማጭበርበር የሚሞክሩ ግለሰቦች ሲያጋጥሙት በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታ እና የደኅንነት አካላት መረጃ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል፡፡

ለዚህም በተቋሙ ነፃ የስልክ መስመር 910 ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል ነው የተገለጸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.