Fana: At a Speed of Life!

በቦረና ዞን የገበያ ትስስር ባለመኖሩ አርብቶ አደሮች እንስሳቶችን በመሸጥ የተጋረጠባቸውን ችግር መቋቋም እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦረና ዞን የገበያ ትስስር ባለመኖሩ አርብቶ አደሮች ከድርቁ የተረፉ እንስሳቶችን በመሸጥ የተጋረጠባቸውን ችግር መቋቋም እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ተገለጸ።

አምና የገበያ ትስስር ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከሌሎች ጋር ለመፍጠር ቢሞከርም በታሰበው ልክ ውጤት እንዳላመጣ የዞኑ የንግድ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሁሴን ሀጂ ተናግረዋል።

ይህ በመሆኑ ምክንያትም በአርብቶ አደሩ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ከፍ አድርጎታል ነው ያሉት።

ዞኑ ለአርብቶ አደሩ የገበያ ትስስር ለመፍጠር አሁንም ጥረት እያደረገ መሆኑን በመጥቀስም፥ በድርቁ ምክንያት በዞኑ ካለው 7 ነጥብ 2 ሚሊየን የእንስሳት ሀብት ወደ 3 ነጥብ 3 ሚሊየኑ ማለቁን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 85 በመቶው የቀንድ ከብት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አርብቶ አደሮች በበኩላቸው አንድ የቀንድ ከብት ለአንድ ኩንታል በቆሎ መግዣ በማያወጣ ዋጋ እንደሚሸጥ ይናገራሉ።

በዞኑ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ እንስሳቱ በመክሳታቸው ገዢ ማጣታቸውንና የሚናገሩት አርብቶ አደሮች፥ ለገበያ የሚያቀርቧቸውን የቀንድ ከብቶች ገዢ በማጣታቸው ምክንያት አንዳንዶቹ ለገበያ ያወጣቸውን የቀንድ ከብቶች እዛው ጥለው እንደሚመለሱ ገልጸዋል።

አሁን ላይ እስከ 500 ብር ድረስ የሚሸጥ ከብት እንዳለና በድርቁ በጣም ያልተጎዱ ከብቶች ደግሞ ገዢ ከተገኘ ከ2 ሺህ እስከ 4 ሺህ ብር ሊሸጡ እንደሚችልም ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት።

ከቀንድ ከብት ባለፈም የግመል ዋጋ ከድርቁ በፊት ከነበረው በእጥፍ በላይ መውረዱን አስረድተዋል።

በዚህም ከዚህ ቀደም ከ70 ሺህ እስከ 90 ሺህ ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ግመል ከ30 ሺህ ብር በታች እየተሸጠ ብለዋል።

በታሪኩ ለገሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.