Fana: At a Speed of Life!

የቃሊቲ- ቂሊንጦና የቃሊቲ -ቱሉ ዲምቱ መንገድ ግንባታ አለመጠናቀቅ ለዘርፈ ብዙ ችግር እንደዳረጋቸው ነዋሪዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሦስት ዓመታት ይጠናቀቃሉ ተብለው በ2010 ዓ.ም የተጀመሩት የቃሊቲ- ቂሊንጦ እና የቃሊቲ -ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች አሁንም ባለመጠናቀቃቸው ለዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተዳረጉ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
 
በወቅቱ በ4 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነቡት እና ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍኑት የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ለመዲናዋ ብሎም ለሀገር በርካታ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ይኖራቸዋል ተብሎም ነበር፡፡
 
ይሁን እንጂ በ3 ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ዕቅድ ተይዞላቸው የነበረው እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች አሁንም ባለመጠናቀቃቸው ለመንገድ መዘጋጋት ምክንያት በመሆን ተሽከርካሪ ውስጥ ለሠዓታት ማሳለፍ የበርካርታ ነዋሪዎች የዕለት ተግባር መሆኑ ተመላክቷል፡፡
 
ፕሮጀክቶቹ በሚገነቡበት ስፍራ ተሽከርካሪ እንደልብ ማግኘት የማይታሰብ እና ለሰዓታት ተሰልፎ ታክሲ መጠበቅም የተለመደ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
 
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በስፍራው ተገኝቶ ባደረገው ቅኝትም ÷ መንገዶቹ በሚገነቡበት አካባቢ ያለው የትራፊክ መጨናነቅ፣ የ”ታክሲ አጣን” ምሬት እና ረጃጅም ሰልፎችን ጨምሮ የአሽከርካሪዎች ቅሬታ ከፍተኛ መሆኑን ታዝቧል፡፡
 
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ታከለ ሉላና በበኩላቸው ÷ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶቹን በተያዘው በጀት ዓመት ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
አሁን ላይ የቃሊቲ -ቂሊንጦ መንገድ ግንባታ አፈጻጸም 61 በመቶ የደረሰ ሲሆን የቃሊቲ- ቱሉ ዲምቱ ደግሞ 76 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል፡፡
 
መንገዶቹ በሁለት በኩል በአንድ ጊዜ ሦስት ተሽከርካሪዎችን ማሳለፍ እንዲችሉ ተደርገው እየተገነቡ ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ ÷ ከ 320 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ድልድይን ጨምሮ የወንዝ ላይ ድልድዮችን ግንባታዎች ያካተቱ መሆናቸውኑም አንስተዋል፡፡
 
በዚህ ዓመት መጨረሻ የመንገዶቹን የመጀመሪያ ደረጃ የአስፓልት ንጣፍ ሥራ በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እና የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
 
የእግረኛ መንገድን ጨምሮ የሳይክል መንገድ እና በግንባታው የተካተቱ ቀሪ ስራዎች ወደ ቀጣይ ዓመት እንደሚሸጋገሩም ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም አስተያየት ሰጪዎች ለግንባታው ትኩረት መስጠትና ክትትል እንደሚያስፈልገው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
 
በዙፋን ካሳሁን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.