Fana: At a Speed of Life!

የግለሰብ መኖሪያ ቤት ኅጋዊ ባልሆነ የመንደር ውል በ11 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሸጡ ተከሳሾች የሙስና ወንጀል ክስ በንባብ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግለሰብ መኖሪያ ቤትን በሀሰተኛ ሠነድ በመንደር ውል በ11 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሸጠዋል የተባሉ አምስት ተከሳሾች ላይ የቀረበ የሙስና ወንጀል ክስ በንባብ ተሰማ።

የአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 05 የወሳኝ ኩነት ጽ/ቤት ሲስተም አድሚኒስትሬተር እና የአቃቂ ቃሊቲ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት የቅየሳ ባለሙያን ጨምሮ አምስት ተከሳሾች የቀረበባቸው ክስ ነው በችሎት በንባብ የተሰማው።

ተከሳሾቹ 1ኛ የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ወረዳ 05 የወሳኝ ኩነት ጽ/ቤት ሲስተም አድሚኒስትሬተር ዳንኤል ተስፋዬ ፣ 2ኛ ተከሳሽ የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት ረዳት የቅየሳ ባለሙያ ያሬድ በየነ ዴንሳ ፣ 3ኛ ተከሳሽ የዱከም ነዋሪ የሆነው አድማሱ ሙላቱ እና በግል ስራ ይተዳደራሉ የተባሉት 4ኛ ተከሳሽ እስራኤል ደጀኔና 5ኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ዳግም ናቸው።

ተከሳሾቹ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) አንቀጽ 33 እና የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1) (ሐ)(2) በመተላለፍ በአራት ተደራራቢ ክስ በየተሳትፎ ደረጃቸው ተጠቅሶ ቀርቦባቸዋል።

በተለይም በአንደኛው ክስ ላይ እንደተጠቀሰው፤1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ከ3ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ወረዳ 05 የቤት ቁጥር 272 ተብሎ የተመዘገበ የግል ተበዳይ ግለሰብን መኖሪያ ቤት በህገወጥ መንገድ በሀሰተኛ ሰነድ በመሸጥ ለግል ጥቅም አውለዋል ተብለው ተከሰዋል።

በዚህም 1ኛ ተከሳሽ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ምዝገባና የመታወቂያ አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 3/2010 ድንጋጌን በመተላለፍ በግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ/ም በወረዳው ኗሪ ላልሆነ 3ኛ ተከሳሽ ለሆነው አድማሱ ሙላቱ በሀሰተኛ ስም ማለትም ገ/እግዛብሔር ገ/ማርያም በሚል በሀሰት ስም የኗሪነት መታወቂያ መስጠቱ በክሱ ተጠቅሷል።

2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በመስከረም 25 ቀን 2015 ዓ/ም የይዞታ የቦታ አቀማመጥ የሚያሳይ ንድፍ አዘጋጅቶ ለ3ኛ ተከሳሽ በመስጠት ለአገልግሎቱ ከ3ኛ ተከሳሽ በአራተኛ ተከሳሽ በዳሸን ባንክ በተከፈተ ሒሳብ አጠቃላይ 350 ሺህ ብር ጉቦ በማስገባት ያልተገባ ጥቅም የተቀበለ መሆኑ በክሱ ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የስራ ሃላፊነታቸውን ለህገወጥ ተግባር በመጠቀም በወንጀሉ ልዩ ተካፋይ በመሆን እርስ በርስ በመመሳጠር የቤት ሽያጭ ውል በመፈጸም ያልተገባ ጥቅም አግኝተዋል ተብለው ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም በከባድ ሙስና ወንጀል ነው የተከሰሱት።

በሁለተኛ ክስ ደግሞ በ3ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን ተከሳሹ ከ2ኛ እና ከ1ኛ ተከሳሾች ያገኘውን መረጃ እና ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም በሐምሌ 11 ቀን 2014 ዓ/ም በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 05 የሚገኘውን የቤት ቁጥር 272 የሆነውን የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤትን በነሃሴ 4 ቀን 2005 ዓ/ም የተሰጠኝ የይዞታ ማረጋገጫ ነው በማለት ትክክለኛውን ካርታ ከማህደር በማስወጣት በሀሰተኛ ስም የተሰራውን ካርታ ወደ ማህደር እንዲገባ ማስደረጉ በክሱ ተጠቅሷል።

ከዚህም በኋላ በፌደራል ሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ቅርጫፍ 7 ጽ/ቤት በአካል በመቅረብ ለሌላኛዋ የግል ተበዳይ ወ/ሮ ቤተልየም ወጋየሁ ሙሉ የውክልና ስልጣን በመስጠት በጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ/ም በመንደር የቤት ሽያጭ ውል በ11 ሚሊየን 500 ሺህ ብር በመስማማት በቅድመ ክፍያ 5 ሚሊየን 300 ሺህ ብር የወሰደ መሆኑ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም ይኸው 3ኛ ተከሳሽ በሃሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል እንዲሁም በሌላ ሰው ስም በሀሰት በመጠቀም ያለፍቃድ ስምን በመለወጥ ወይም በሌላ ሰው ስም መጠራት የደንብ መተላለፍ ወንጀል ተከሷል።

በሌላኛው ክስ ደግሞ ከ3ኛ እስከ 5 ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ድንጋጌን በመተላለፍ በተለያዩ ቀናቶች የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ከባንክ ወጪ በማድረግ ለግል ጥቅም አውለዋል ተብለው ተከሰዋል።

ከ4ኛ ተከሳሽ በስተቀር ሁሉም ተከሳሾች ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን÷ችሎቱም በዓቃቢህግ ተሻሽሎ የቀረበውን ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስን በንባብ ዛሬ አሰምቷል።

ክሱን በንባብ ያሰማው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5 ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ክሱ በንባብ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾቹ ”ወንጀሉን አልፈጸምንም ”ሲሉ ገልጸው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ለችሎቱ አስረድተዋል።

ከሳሽ ዐቃቢህግ በበኩሉ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ምስክሮች ይሰሙልኝ ሲል ጠይቋል።

ችሎቱም የዓቃቢህግ ምስክርን ለመጠባበቅና ለመጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

4ኛ ተከሳሽ የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግለት ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.